❖ ልዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በዘመነ ኮሮና ቫይረስ

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ባስከተለው ችግር ምክንያት ብዙዎቻችን በተለይም ተማሪዎች እቤት ውስጥ እንድንቀመጥ ተገድደናል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ጊዜው መንፈሳዊ ሕይወታችን ለማጠናከር እንጸልይበታለን፤ መጽሐፍ ቅዱስም እናነብበታለን፤ እንማርበታለን፡፡ በመሆኑም የተወሰነው ጊዜአችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ለማሳለፍ ይረዳን ዘንድ የሀገረስብከታችን ሐዋርያዊ የሥራ መምሪያ የሚከተለውን ትምህርት አዘጋጅቶልናል፡፡ ትምህርቱን በሚገባ አንብበን ጥያቄዎቹን እንመልስ፡፡ ሙሉ ምላሽ ለምታገኙ ሁሉ በያላችሁበት አወዳድረን አሸናፊ ለሆኑት ልዩ ሽልማት በያላችሁበት ለማድረስ እንሞክራለን፡፡  

 ጥያቄዎቹ የሚመሉበት የመጨረሻው ቀን … ግንቦት 30/ 2012 ዓ.ም. ይሆናል፡፡    መልካም ንባብ

የዮሐንስ ወንጌል


❖ ወንጌላዊው ዮሐንስ ማን ነው?

ዮሐንስ የሚለው ስም የግሪክ ቃል ሲሆን “የሆሐናን” ወይም “ዮሐናን” ከሚለው የዕብራይስጥ ስም የተገኘ ነው፡፡ በዕብራይስጥ “ዮሐናን” የሚለው ስም “እግዚአብሔር ጸጋን አጐናጸፈ” ወይም “እግዚአብሔር ጸጋን ሰጠ” ወይም “እግዚአብሔር ጸጋን አደረገ” ማለት ነው፡፡ አዲስ ኪዳን ውስጥ ዮሐንስ በሚለው ስም ከተሰየሙት ውስጥ ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት መካከል አንዱ የነበረው ዮሐንስ ነው፡፡ በኋላ ግን ይህ ዮሐንስ ከመጥምቁ ዮሐንስ የተለየ መሆኑን ለመግለጽ “ወንጌላዊው ዮሐንስ” በመባል መጠራት ጀመረ፡፡ ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ የሆነው ዮሐንስ የዘብዴዎስና ምናልባትም የሰሎሜ ልጅ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል(ማቴ 4፡ 21)፡፡ 

ዮሐንስ ከአባቱ ከዘብዴዎስና ከታላቅ ወንድሙ ከያዕቆብ ጋር ዓሣ በማጥመድ ሥራ ላይ እያሉ ኢየሱስ እንዲከተሉትና ሰዎችን በማጥመድ ሥራ ላይ እንዲሠማሩ ጠራቸው (ማር 1፡ 19፤ ሉቃ 5፡ 10)፤ የነጐድጓድ ልጆች ብሎም ሰየማቸው(ማር 3፡ 17)፡፡ 

በሐዋርያዊ ሕይወቱ ውስጥ ዮሐንስ ከወንድሙ ከያዕቆብና ከሌላው ደቀ መዝሙር ከጴጥሮስ ጋር በመሆን በተለያየ ቦታ ከክርስቶስ ጋር በልዩ መልኩ ይገኙ ነበር፡፡ ከእነዚህም ቦታዎችና ሁኔታዎች መካከል የኢየሱስ ፊት እንደ ፀሐይ ያበራበትና ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆኖ ያንጸባረቀበት ተራራ ላይ(ማቴ 17፤ ማር 9)፣ ኢየሱስ በስምዖንና እንድርያስ ቤት በተገኘበት ጊዜ(ማር 1፡ 29)፣ ወደ አንድ የምኵራብ አለቃ ቤት በገቡበት ሰዓት(ማር 5፡ 37) እንዲሁም ከትንሣኤው በኋላ ለሰባቱ ደቀ መዛሙርት በተገለጠላቸው ጊዜ የሚሉትን ተጠቃሾች ናቸው(ዮሐ 21፡ 2)፡፡

❖ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወንጌላዊው ዮሐንስ ከኢየሱስ ጋር የነበረው ቀረቤታና ወዳጅነት በምን መልክ ተገልጿል?

ዮሐንስና ያዕቆብ ከሌሎች ሐዋርያት ለየት ባለ መልኩ ወደ ክርስቶስ በመቅረብ ይወያዩና ጥያቄዎች ይጠይቁት ነበር፡፡ ዮሐንስ ወደ ኢየሱስ ቀርቦ “መምህር ሆይ! አንድ ሰው በስምህ አጋንንት ሲያስወጣ አየን፤ ከእኛም ጋር ስላልሆነ ከለከልነው” አለው(ማር 9፡ 38)፡፡ ያዕቆብና ዮሐንስ ወደ ኢየሱስ ቀርበው “በመንግሥትህ ክብር አንዳችን በቀኝህ፣ አንዳችን በግራህ እንድንቀመጥ ፍቀድልን” አሉት(ማር 10፡ 37)፡፡ ኢየሱስ በደብረዘይት ተራራ ተቀምጦ ሳለ ዮሐንስ ከሌሎች ሦስት ሐዋርያት ጋር በመሆን ስለ ዓለም መጨረሻ ጠየቁት(ማር 13፡ 3)፡፡ የሰማርያ ሰዎች ኢየሱስን መቀበል እንዳልፈለጉ ያዕቆብና ዮሐንስ በተረዱ ጊዜ ከሰማይ እሳት ወርዶ የሰማርያ ሰዎች ያቃጥላቸው ዘንድ ማዘዝ እንዲችሉ ከኢየሱስ ፈቃድ ጠየቁ(ሉቃ 9፡ 54)፡፡ 

በመጨረሻም ኢየሱስ በጸለየበት እንዲሁም ማዘንና መጨነቅ በጀመረበት ጌተሴማኒ አጠገቡ ከነበሩት ሦስት ደቀ መዛሙርት መካከል አንዱ ዮሐንስ ነበር (ማቴ 26፡ 37)፡፡ ከእነዚህ ንባባት እንደምንረዳው ዮሐንስ ከኢየሱስ ጋር ይጓዝ የነበረ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች በተለየ መልኩ ልዩ ወዳጅነት እንደነበረውም ጭምር ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ምንም እንኳ ስሙ በግልጽ ባይጠቀስም “ኢየሱስ የሚወድደው ደቀ መዝሙር” በሚል የተገለጸው የዘብዴዎስ ልጅ ዮሐንስ ሊሆን እንደሚችል ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ኢየሱስ የመጨረሻው ራት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በበላበትና እግራቸውን ባጠበበት ምሽት ይወድደው የነበረው ደቀ መዝሙር አጠገቡ ተቀምጦ ነበር፡፡ በዚህ ምሽት ኢየሱስ አሳልፎ ስለሚሰጠው ሰው በተናገረ ጊዜ የሚወድደው ደቀ መዝሙር ወደ ኢየሱስ ጆሮ ተጠግቶ ጌታ ሆይ! አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው? ሲል ጠየቀው (ዮሐ 13፡ 23፤ ዮሐ 21፡ 20)፡፡ ይህ ክርስቶስ የሚወድደው ደቀ መዝሙር በዮሐንስ ወንጌል መጨረሻ ላይ “ስለ እነዚህ ነገሮች ሁሉ የመሰከረና እነዚህንም ነገሮች የጻፈ ይህ ደቀ መዝሙር ነው፤ የእርሱም ምስክርነት እውነት እንደሆነ እናውቃለን” በማለት ተገልጿል(ዮሐ 21፡ 24)፡፡ 

በአጠቃላይ ምንም እንኳ ስሙ በግልጽ ዮሐንስ ተብሎ ባይጠቀስም ኢየሱስ ይወድደው የነበረው ደቀ መዝሙር አራተኛውን ወንጌል የጻፈው የዘብዴዎስ ልጅ ዮሐንስ ሊሆን እንደሚችል ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ እርሱም ከኢየሱስ ጋር ቅርበትና ወዳጅነት የነበረው ነው፡፡

❖ የዮሐንስ ወንጌል ከሌሎቹ ሦስቱ ወንጌላት ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?       

የዮሐንስ ወንጌል በአጻጻፍ ስልቱ ገና ከወንጌሉ መጀመሪያ ለየት ያለ መሆኑን በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ሦስቱ ወንጌላውያን የሚጀምሩት በኢየሱስ የዘር ሐረግ ዙሪያና በመጥምቁ ዮሐንስ መወለድ ጋር የተያያዙ ነገሮች ላይ አጠር ያለ መግቢያ በመስጠት ነው፡፡ ዮሐንስ ግን ኢየሱስ ገና ጥንት ዓለም ከመፈጠሩ በፊት በእግዚአብሔር ዘንድ እንደነበረና ሁሉም ነገር በእርሱ እንደተፈጠረ በመግለጽ ነው፡፡ በአጻጻፍ ሂደቱም ላይ በጥንቃቄና ጥበብ በተሞላበት መልኩ የተጻፈ መሆኑን ከወንጌሉ ይዘት መረዳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በአይሁዳውያን ዘንድ ፍጽምና የሚያመለክተውን ሰባት(7) ቁጥርንና ሙልአትን የሚያለክተው ሦስት(3) ቁጥርን በመጠቀም የተለያዩ መልእክት አዘል ትምህርቶችን ያስተላልፋል፡፡

ገና ከወንጌሉ መጀመሪያ ኢየሱስ መለኮታዊ ቃልና ራሱ እግዚአብሔር እንደሆነ በግልጽ ይናገራል፡፡ በዚህም ከሦስቱ ወንጌላውያን በተለየ መልኩ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር አብ ጋር ያለውን ጥብቅ የሆነ ወዳጅነትና ቀረቤታ ያሳያል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ኢየሱስ ለሰዎች የቅርብ ወዳጅ እንደሆነና ማደሪያውም በእነርሱ መካከል እንዳደረገ ያስገነዝባል፡፡ ነገር ግን ዮሐንስ የኢየሱስ ልደት ወይም የትውልድ ሐረግም ሆነ ጥምቀት አይገልጽም፡፡ ኢየሱስ ቀድሞ በቃል መልክ በእግዚአብሔር ዘንድ የነበረ፣ ሁሉ ነገር በእርሱ የተፈጠረ፣ ከተፈጠረው ሁሉ አንድም ነገር ያለ እርሱ የተፈጠረ እንደሌለ፣ ሥጋ ለብሶ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በሰዎች ዘንድ ያደረ መሆኑን ይናገራል፡፡ ኢየሱስ ዘላለማዊ የሕይወት ቃል ነው፤ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፤ ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ ነገር ግን ራሱን ሙሉ በሙሉ ለእግዚአብሔር አብ ታዛዥነት ያደረገ ነው፡፡

በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ኢየሱስ ያከናወናቸው ምልክቶች ተብለው የተጠሩት ተአምራት ሰባት ናቸው፡፡ የተአምራቶቹ ዋና ዓላማ ደቀ መዛሙርቱንና ሕዝቡን እንዲያምኑ ወይም እምነታቸውን እንዲያጠናከሩ የተከናወኑ ናቸው፤ ምክንያቱም በእያንዳንዱ ተአምር በስተመጨረሻ ላይ “በእርሱም አመኑ” የሚሉት ቃላት እናገኛለን (ዮሐ 2፡ 11፤ 4፡ 53)፡፡ በተጨማሪም የተአምራቶቹ ሌላው ዓላማ ሕዝቦች ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን እንዲያውቁ፣ እንዲያምኑና ሕይወት እንዲያገኙ ነው፡፡

አራቱም ወንጌላውያን ስለ ኢየሱስ ማንነት ሲያስተምሩና ሲመሰክሩ በተለያየ መልኩ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍትን ይጠቅሳሉ፡፡ ዮሐንስ ግን ከማናቸውም በላይ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት በስፋት መጥቀሱ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱን ነገር የኢየሱስ መሲሕነት በሚያረጋግጥና ትርጉም በሚሰጥ መልኩ ያደረገው መሆኑን ነው፡፡ በዚህም መሠረት ብሉይ ኪዳን ውስጥ ቀድሞ የተገለጹት ነገሮች በመውሰድ ለኢየሱስ ተግባራዊ ያደርገዋል፡፡ ለምሳሌ የእግዚአብሔር በግ(ዮሐ 1፡ 29)፣ አዲሲትዋ ቤተ መቅደስ(2፡ 21)፣ ሙሴ በበረሐ የሰቀለው ፈዋሽ የሆነው እባብ(3፡ 14)፣ የሕይወት እንጀራ ወይም ከሰማይ የወረደ መና(6፡ 35)፣ መልካሙ እረኛ(10፡ 11)፣ እውነተኛው የወይን ግንድ(15፡ 1) የሚሉትን ከብሉይ ኪዳን በመጥቀስና ከኢየሱስ ማንነትና ትምህርት ጋር በማያያዝ ያብራራል፡፡

የኢየሱስ ሕማማትና ሞት ባካተተው ክፍል ውስጥ በሦስቱ ወንጌላውያን ያልተጠቀሱ፤ ነገር ግን ዮሐንስ ልዩ ትኩረት የሚሰጣቸው ነገሮች አሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በዮሐንስ ወንጌል ብቻ ተጠቅሰው ከሚገኙት መካከል የተወሰኑትን እንደሚከተለው ይቀርባሉ፡፡

  • ኢየሱስ መስቀሉን ያለማንም እርዳታ ብቻውን መሸከሙን (ቀሬናዊው ስምዖን አልተጠቀሰም) ፤

  • የአይሁድ ንጉሥ ኢየሱስ የሚለው ጽሑፍ በሦስት ቋንቋ መጻፉ (ዮሐ 19፡ 20)፤

  • እናቱን ማርያምና የሚወድደው ደቀ መዝሙር መስቀሉ ሥር ሆነው እንደተናገራቸው (ዮሐ 19፡ 26)፤

  • ሆምጣጤ በሂሶጵ እንጨት ተንጠልጥሎ መሰጠቱን (ዮሐ 19፡ 29)፤

  • ኢየሱስ ሆምጣጤውን ከቀመሰ በኋላ “ተፈጸመ” ብሎ መሞቱን (ዮሐ 19፡ 30)፤

  • ጐኑን በጦር መወጋቱንና ደምና ውሃ መውጣቱን (ዮሐ 19፡ 34)፤

  • አርማቲያው ዮሴፍ ብቻ ሳይሆን ኒቆዲሞስም ጭምር ቀብሩ መፈጸሙን (ዮሐ 19፡ 38)፤

  • ኒቆዲሞስ 25 ኪ.ግ. የሚያህል የከርቤና የሬት ቅልቅል ይዞ መምጣቱን የሚሉት ናቸው (ዮሐ 19፡ 39)፡፡

❖ በእግዚአብሔር ዘንድ የነበረው ቃል (ዮሐ 1፡ 1-18) ፤ ይህ “ቃል” ምንድን ነው?

ወንጌሉ ሲጀምር “ቃል በመጀመሪያ ነበረ” ይላል፡፡ የዚህ አባባል ምሥጢር በሚገባ ለመረዳት “ቃል” እና “መጀመሪያ” የሚሉት ሁለት ቃላት በደንብ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ጸሐፊው እነዚህ ሁለት ቃላት ለምን መጠቀም ፈለገ? በወቅቱ በእነዚህ ቃላት አማካይነት ይነገሩ የነበሩ አፈ ታሪኮች ወይም በሌሎች የሚሰጡ ትምህርቶች ነበሩን? የሚሉትንና ተመሳሳይነት ያላቸው ጥያቄዎች ለመረዳት መሞከሩ ወንጌላዊው በእነዚህ ሁለት ቃላት ተጠቅሞ ማስተላለፍ የፈለገውን ትምህርት ለመረዳት ወሳኝነት አለው፡፡

በግሪክ ፍልስፍና ውስጥ በተለይም “እስቶይክስ” በተባሉት ዘንድ “ቃል” ራሱ ፍጹም የሆነና ምንም ዓይነት እንከን በማይወጣለት ሁኔታ ዓለምን የሚያንቀሳቅስ ኃይል እንደሆነ የሚገልጽ እምነት ተንሰራፍቶ ነበር፡፡ በዚሁ በፍልስፍናው ዓለም አልፎ አልፎ ይህ “ቃል” ልዩ ስጦታ፣ ዕውቀትና ችሎታ ላላቸው ሰዎች በመጠሪያነት ይጠቀሙበት ነበር፡፡ “ግኖስቲክስ” በተባሉት እንቅስቃሴ ውስጥ በትውፊት መልክ ከሚነገሩት ውስጥ አንዱ “ቃልን” በተመለከተ ነው፡፡ በዚህም መሠረት “ቃል” ከሰማይ የተላከ፣ ዓለምንና በውስጥዋ የሚገኙትን ፍጥረታት ሁሉ ለማዳን የሚችል ልዩ ኃይል ያለው እንደሆነና ወደፊት እንደሚመጣ ተገልጿል ፡፡  

በብሉይ ኪዳን ውስጥ “የእግዚአብሔር ቃል” በተደጋጋሚ ተጠቅሷል፡፡ ለምሳሌ ከእግዚአብሔር አንደበት የሚወጣው ቃል እግዚአብሔር የሚሻውን ሁሉ ምድር ላይ ሳያከናውንና ተልእኮውን ሳይፈጽም በከንቱ ወደ እግዚአብሔር እንደማይመለስ ከነቢዩ ኢሳይያስ እንረዳለን(ኢሳ 55፡ 10-11)፡፡ ነገር ግን ይህ ቃል እንደ መልእክት ነው እንጂ ባሕርይ እንዳለው እንደ አንድ ግዙፍ አካል እንደተላበሰ ሆኖ አልተገለጸም፡፡ በመጽሐፈ ሲራክ ውስጥ “ጥበብ” መኖርያዋ በሰዎች መካከል ለማድረግ ቦታ ትፈልግ እንደነበር፣ ስለ ራስዋ እንደምትናገር እንዲሁም ማንነትዋን ለሰዎች እንደምትገልጽ ተጠቅሶአል፡፡ ይህች “ጥበብ” ለየት የሚያደርጋት ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ስለራስዋና ስለ ሌሎች ትናገራለች፤ በሕዝቦች መካከል ትኖራለች፤ በእግዚአብሔር ፊት ትቆማለች፤ በሰማይና በምድር ምንም ወሰን ሳይኖራት ትገኛለች፤ የሚታዘዙዋትም ይባረካሉ(ሲራ 24)፡፡ 

በሌላ በኩል ደግሞ ይህች “ጥበብ” “ቃል” ከሚለው ጋር ግኑኝነት እንዳለው ከመጽሐፈ ጥበብ እንገነዘባለን፡፡ መጽሐፈ ጥበብ በቃልህ ዓለምን ፈጥረሃል፤ በጥበብህ ሰውን ፈጥረሃል ይላል(ጥበ 9፡ 1-2)፡፡ በተጨማሪም ይህ ጥበብ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደተገኘ ወይም እንደወጣ ይናገራል(ሲራ 24፡ 3)፡፡ በአይሁዳውያን ዘንድ ስለ ጥበብ ከተብራራው ሰፋ ያለ ትንታኔ መረዳት የሚቻለው ጥበብ በእግዚአብሔር የተፈጠረ ነው፡፡ ቃል ግን ቀድሞም የነበረ በመሆኑ ምክንያት ከጥበብ ጋር ያላቸው ልዩነት የሰፋ ነው፡፡     

በአዲስ ኪዳን ውስጥ ቃል በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ካልሆነ በስተቀር የትም ቦታ አልተጠቀሰም፡፡ በእርግጥ “የእግዚአብሔር ቃል” በደም የተነከረ ልብስ እንደለበሰ ተጠቅሶ እናገኘዋለን(ራእ 19፡ 13)፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ “የሕይወት ቃል” ተብሎ በዮሐንስ መልእክት ውስጥ ሁለት ጊዜ ተጠቅሶአል(1ዮሐ 1፡ 1-2)፡፡ በሌላ ቦታ ግን ለየት ባለ መልኩ የእግዚአብሔር ቃል እንደ መልእክት ሆኖ ሰዎች እንዲናገሩት እንደመጣ ይገልጽልናል(ሉቃ 3፡ 2)፡፡ ጳውሎስ ደግሞ ለተጠሩት ግን ለአይሁዳውያንም ሆነ ለግሪካውያን ክርስቶስ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ ነው በማለት ክርስቶስ ከጥበብ ጋር አያይዞ ይገልጸዋል(1 ቆሮ 1፡ 24)፡፡ 

በአጠቃላይ ወንጌላዊው ዮሐንስ በቃልና በጥበብ ዙሪያ የተጻፉትንና የተነገሩትን የግሪክ ፍልስፍና፣ የብሉይ ኪዳን አገላለጾች በተለይም በመጽሐፈ ሲራክና በመጽሐፈ ጥበብ ውስጥ የነበሩትን በማገናዘብ “ቃል” የሚለውን ለየት ያለ ተጨማሪ ትርጉም በመስጠት ሥጋ በለበሰ መልኩ ወደ ሰዎች እንደመጣ ይገልጻል፡፡ በመሆኑም ይህ “ቃል” ቀድሞ የነበረ አሁን ግን ግዙፍ ሆኖ በሰዎች ዘንድ ለማደር እንደመጣ ያስገነዝባል፡፡

❖ “በመጀመሪያ” ሲል ምን ማለት ነው?

  ቀጥሎም ወንጌላዊው “ቃል በመጀመሪያ ነበረ” ሲል ይህ መጀመሪያ መቼ ነው? የምንስ መጀመሪያ ነው? ጀማሪውስ ማን ነው? የሚሉት ጥያቄዎች ይነሣሉ፡፡ 

በኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ ጅማሬ ላይ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” ይላል(ዘፍ 1፡ 1)፡፡ በዚህም እግዚአብሔር አንድን ነገር አከናውኖ ወይም ፈጥሮ እንዳጠናቀቀ ይገልጻል፡፡ ይህ የተከናወነው ነገር ጅማሬ ወይም መነሻ የሚሆን መሠረት አለው እንደማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፈ ጥበብ ሰፋ ባለ መልኩ ስለ ጥበብ ከተናገረው የተወሰነ ግንዛቤ እናገኛለን፡፡ ጥበብ እንዲህ ትላለች፤ “እግዚአብሔር ከሁሉ በፊት ፈጠረኝ፤ ከጥንት ጀምሮ የሥራው ተቀዳሚ አደረገኝ፤ በጥንት ዘመን ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ በመጀመሪያ ተሾምሁ”(ምሳ 8፡ 22-23፤ ሲራ 24፡ 9)፡፡ እዚህም ላይ ጥበብ ከሁሉ በፊት መፈጠርዋንና መሠረትዋ እግዚአብሔር እንደሆነ ነው፡፡ ወንጌሉ የሚለው ግን ተፈጠረ ወይም ተጀመረ ሳይሆን “ቃል ነበረ” በማለት ቀድሞ እንደነበረ ያመለክታል፡፡ ከፍጥረታት ሁሉ በፊት ተጀመረ ወይም ተፈጠረም አይልም፡፡ 

“በአጠቃላይ የጊዜ ጉዳይ ሳይሆን ከጊዜ ውጭ በሆነ መልኩ የመሆን ወይም የመኖር ነገር ነው፡፡ የዚህ ነገር መኖርና መሆን ደግሞ ከእግዚአብሔር የመሆን ወይም የመኖር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን ከጊዜ ጋር የተያያዘውን አገላለጽ እንደ ዮሐንስ ባይገልጸውም “የፍጥረት ሁሉ በኩር ነው” ይለዋል(ቆላ 1፡ 15)፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ከፍጥረታት ሁሉ በፊት ነው እንደማለት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ የሐዋርያው ጳውሎስ አባባል ኢየሱስ ከፍጥረታት በፊት ተፈጠረ ወደሚለው ወደ ተሳሳተ ግንዛቤ ሊያደርሰን ይችላል፡፡ ዮሐንስ የፈለገው ግን ከጊዜ ውጪ የሆነና ያልተፈጠረ የሚለውን ነው፡፡ ይህንን አመለካከት የበለጠ ሲገልጸው “ሁሉን ነገር በእርሱ ተፈጠረ፤ ከተፈጠረውም ሁሉ አንድም ነገር ያለ እርሱ የተፈጠረ የለም” ይላል(ዮሐ 1፡ 3)፡፡  

በማያያዝም ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ይህም ቃል እግዚአብሔር ነበረ ይላል (ዮሐ 1፡ 1)፡፡ ይህም ማለት በመጀመሪያ “ቃል” እና “እግዚአብሔር” አብሮ የመኖራቸው ብቻ ሳይሆን የጠበቀ ወዳጅነታቸው፣ ቀረቤታቸውና አንድነታቸው የሚገልጽ ነው፡፡ አንድነታቸው የጠበቀ እንደሆነና ልዩነትም እንዳላቸው ያስገነዝበናል፡፡ 

“ቃል በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ” ሲል የእግዚአብሔር አባትነት ይገልጻል፤ ቃሉ ደግሞ ማደሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ መሆኑን ከማሳየቱም በላይ አንድነቱንና ኅብረቱን ያሳያል፡፡ የእግዚአብሔር አባትነት ደግሞ ቃል የነበረውን ሥጋ ለብሶ፣ ተልእኮ ይዞ እንዲንቀሳቀስ ወይም ወደ ሰዎች ዘንድ እንዲመጣ ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ “ይህ ቃል በእግዚአብሔር ዘንድ ነበር” በሚል መልኩ ብቻ አልቀረም፤ ሥጋ ለብሶ፣ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ ማደሪያውን በሰዎች ዘንድ ሊያደርግ መጣ፡፡
 

❖ “በእርሱ ሕይወት ነበረች” ሲል እንዴት እንረዳዋለን? ምን ዓይነት ሕይወት ነው የነበረው?

ወንጌላዊው በእርሱ ሕይወት ነበረች፤ ይህች ሕይወት የሰዎች ብርሃን ነበረች ይላል (ዮሐ 1፡ 4)፡፡ በመጀመሪያ በእርሱ ሲል በቃል ውስጥ ሕይወት ነበረች ማለት ነው፡፡ ቃል ከጊዜ ገደብ ውጭ በሆነ ሁኔታ በሕይወት የተሞላ ነው፡፡ ይህ ሕይወት ደግሞ ሌሎችን ሕያው የሚያደርግ እንደሆነ ሲገልጽ “የሰዎች ብርሃን ነበረች” ይላል፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ራሱ ሕይወት ብቻ ሳይሆን ሕይወት ሰጪም እንደሆነ ወንጌላዊው ገና ከመጀመሪያው ይናገራል፡፡ 

ይህንን አገላለጽ ዘግየት ብሎ የበለጠ ግልጽ በሆነ ሁኔታ ያቀርበዋል፡፡

  • አብ ራሱ የሕይወት ምንጭ እንደሆነ፤ ወልድን የሕይወት ምንጭ እንዲሆን አድርጎታል (ዮሐ 5፡ 26)፡፡

  • እኔ የመጣሁት ሕይወት እንዲያገኙና የተትረፈረፈ ሕይወት እንዲኖራቸው ነው (ዮሐ 10፡ 10)፡፡

  • መንገድና እውነት ሕይወትም እኔ ነኝ (ዮሐ 14፡ 6)፡፡

  • ይህ ብርሃን ወደ ዓለም የሚመጣና ለሰው ሁሉ ብርሃን የሚሰጥ እውነተኛ ብርሃን ነበር (ዮሐ 1፡ 9)፡፡

  • የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ፤ እኔን የሚከተል ሁሉ የሕይወት ብርሃን ያገኛል (ዮሐ 8፡ 12)፡፡ 

እግዚአብሔር አብና ጌታ ኢየሱስ ከሰዎች ጋር የሚመሠርቱት ወዳጅነት በሕይወት የተሞላና ሕይወት ከመስጠት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በእርግጥ ዘማሪው አስቀድሞ “አንተ የሕይወት ሁሉ ምንጭ ነህ፤ ከአንተም ብርሃን የተነሣ ብርሃን እናያለን” በማለት ዘምሮ ነበር(መዝ 36፡ 9)፡፡ ብርሃንና ሕይወት የተሞላው ቃል ከእግዚአብሔር አብ ጋር አንድነትና ውሕደት እንዲሁም ራሱ የቻለ ልዩነት ያለው ነው፤ ሕይወትነቱንና ብርሃንነቱን ግን ለራሱ ብቻ ሳይወሰን ከሌሎች የሚካፈለው ወይም ለሌሎች የሚሰጠው ነው፡፡ ይህ ሕይወትና ብርሃን ገና ከጅማሬው “እንደ ሕይወት ዛፍ ፍሬ” ሆኖ ለብዙኃን የሚያገለግል ይሆናል፡፡ 

በአጠቃላይ ይህ ቃል በጊዜና በቦታ ያልተወሰነ፤ ነገር ግን ከዘለዓለም ዓለም የሚኖረው እግዚአብሔር ዘንድ የነበረና አሁን ግን ሥጋ ለብሶ ግዙፍ ሆኖ ሕይወትንና ብርሃንን ይዞ ማደርያውን በሰዎች መካከል ለማድረግ የመጣ ነው፡፡ የመጣውም ልዩ ክብር ተጐናጽፎ፣ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ ነው(ዮሐ 1፡ 14)፡፡ እርሱ እውነተኛ ብርሃን ስለሆነ በዓለም ሁሉ ያበራል(ዮሐ 1፡ 9)፤ ጨለማም ከቶ አያሸንፈውም(ዮሐ 1፡ 5)፡፡ ይህም ማለት የሞትን ኃይል አስሮ ሊያስቀረው አይችልም፤ በጨለማ የተመሰለውን ሞት ድል አድርጎ ዳግመኛ ወደ ሕይወት ይመለሳል፡፡ እርሱን አምነው የተከተሉትም አያፍሩም፤ ይልቅስ በጸጋ ላይ ጸጋ ይቀዳጃሉ(ዮሐ 1፡ 16)፡፡

  በቀድሞ ዘመን እግዚአብሔር ክብሩን በተለያየ ጊዜ በሙሴ በአማካይነት ገለጠ፤ በተለይም በሙሴ በኩል በተሰጠው ሕግ አማካይት ክብሩን ገልጦ ከሰዎች ጋር ወዳጅነት የመመሥረቻ መንገዱን ይበልጥ አሳወቀ(ዘጸ 19-20፤ ዮሐ 1፡ 17)፡፡ አሁን ግን  የእግዚአብሔር ክብር ሥጋ ለብሶ ወደ ሰዎች ዘንድ መጣ፤ በእርሱ አማካይነት ሰዎች የእግዚአብሔርን ክብር ያያሉ፡፡ ይህንንም ሲያረጋግጥ “እግዚአብሔርን ያየው ከቶ ማንም የለም፤ ይሁን እንጂ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ያለው አንድ ልጁ ብቻ ገልጦታል” ይላል(ዮሐ 1፡ 18)፡፡ 

በአጠቃላይ የዮሐንስ ወንጌል መግቢያ ውስጥ በጥልቀት የተተነተነው ምሥጢር እግዚአብሔር ራሱን ለሰዎች እንዴትና በምን ዓይነት መልኩ እንደገለጠና ማደሪያውንም በእነርሱ መካከል እንዳደረገ የሚያሳይ ነው፡፡ በተጨማሪም ሰዎች በእምነት አማካይነት የእግዚአብሔር ልጆች የመሆንን ጸጋ እንደሚቀዳጁና በብርሃን እንደሚኖሩ የሚገልጽ ነው፡፡


ኢየሱስና ማርያም በቃና የሠርግ ግብዣ ቦታ ላይ


❖ ከመጽሐፍ ቅዱስ አኳያ የወይን ጠጅ እንዴት እንረዳዋለን?

ከቅዱሳት መጽሐፍት እንደምንረዳው በአይሁዳውያን ባህል የወይን ጠጅ ክቡር የሆነ መጠጥ፣ በክብር ስፍራ የሚቀርብና የሰውን ልብ ደስ የሚያሰኝ መጠጥ ነው(መሳ 9፡ 13፤ መዝ 104፡ 15፤ ዘካ 10፡ 7)፡፡ እግዚአብሔር በጽዮን ተራራ ላይ ለዓለም መንግሥታት ሁሉ በሚያዘጋጀው ታላቅ ግብዣ መልካም ምግብና ምርጥ የወይን ጠጅ እንደሚያቀርብ ተገልጿል(ኢሳ 25፡ 6)፡፡ ስለዚህ ወይን ጠጅ የሠርጉን ግብዣ ውበት የሚሰጥና ታዳሚዎችንም በሥርዓቱ እንዲደሰቱበት በክብር የሚቀርብ መጠጥ ነው፡፡ 

በቃና የሠርግ ግብዣ ላይ ግን ገና ወይኑ እጅግ በጣም በሚያስፈልግበትና መስተናገድ ባለበት ጊዜ ይመስላል ያለቀው፡፡ ይህ ደግሞ ለሠርጉ ባለቤት አስጨናቂና አስደንጋጭ እንዲሁም አሳፋሪ ነገር ሊሆን ይችላል፡፡ ይህንን ጭንቀት ከማንም በፊት አስቀድማ ተረድታ ለመፍትሔ የፈጠነችው የኢየሱስ እናት ማርያም ናት፡፡ ይህም ማለት በዚያን ቅጽበት ኢየሱስ ድንቅ የሆነውን ነገር ማድረግ እንደሚችል ጠንቅቃ የተረዳችው እርስዋ ብቻ እንደሆነች የሚያስገነዝብ ነው፡፡ በመሆኑም ወደ እርሱ ቀርባ “ወይን የላቸውም እኮ!” አለችው (ዮሐ 1፡ 3)፡፡

ይህ አነጋገርዋ ለሰዎቹ አንገብጋቢ ችግር ልዩ ትኩረት በመስጠትና ያገባኛል በሚል መንፈስ ባዶነታቸውንና ፈጣን የሆነ ምላሽ ፈላጊነታቸውን ለልጅዋ ትገልጽለታለች፡፡ የእርስዋ ዋና ተግባር የሰዎቹን ችግር ለኢየሱስ ማቅረብ ነው፤ የማከናወኑ ተግባር የሚወጣው ግን ኢየሱስ ነው፡፡ ማርታና ማርያም ወንድማቸው አልዓዛር በታመመ ጊዜ ጌታ ሆይ! ወዳጅህ ታሞአል በማለት ወደ ኢየሱስ ላኩበት እንጂ ቶሎ ናና ፈውሰው አላሉትም (ዮሐ 11፡ 3)፡፡ ለኢየሱስ መንገር ወይም የተፈጠረው ችግር ማሳወቅ ብቻ ነው ከሰዎች የሚጠበቀው፡፡ የኢየሱስ እናት ያደረገችውም ይህንኑ ነው፡፡ ኢየሱስም “አንቺ ሴት ! ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም እኮ” በማለት መለሰላት (ዮሐ 2፡ 4)፡፡

❖ “አንቺ ሴት ወይም ሴት ሆይ!” የሚለውን እንዴት እንረዳዋለን?

ይህ የአማርኛ ትርጉም በተለይም “አንቺ ሴት! ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?” የሚለውን ኢየሱስ ማለት የፈለገውን ትክክለኛውን ነገር አይገልጽም፡፡ ወንጌላዊው በግሪክ ቋንቋ ኢየሱስ የተናገረውን እንዲህ ብሎ አስፍሮታል፤ ቲ(ምን) ሞይ(ለእኔ) ካይ(እና) ሶይ(ለአንቺ) ጉናይ? (ሴት ሆይ) ፡፡ ይህ ንግግር በተለያየ ቋንቋ ሲተረጐም ብዙ ልዩነቶችና ስሕተቶች ተከስተዋል፤ አሁንም እየተከሰቱ ነው፡፡ በአማርኛው ቋንቋ እንኳ ቃል በቃል ቢተረጐም መሆን ያለበት “ሴት ሆይ! ይህ ነገር ለእኔና ለአንቺ ምንድን ነው?” ወይም “ሴት ሆይ! ይህ ነገር እኛን በምን መልኩ ይመለከተናል?” ወይም “ሴት ሆይ! ይህ ነገር እኔና አንቺ ይመለከተናልን?” በሚል መልኩ መተርጐም ነበረበት፡፡

በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ኢየሱስ “አንቺ ሴት” ወይም “ሴት ሆይ!” የሚለው ቃል ሁለት ጊዜ እናቱ ማርያምን ለመጥራት ተጠቅሞበታል(ዮሐ 2፡ 4፤ 19፡ 26)፡፡ ይህ ቃል የተግሣጽ፣ የማዋረድ፣ ክብር የማሳጣት አይደለም፤ በእናትና ልጅ መካከል ያለውን ፍቅር አሳንሶ የሚያሳይም አይደለም፡፡ ይህ አጠራር በወቅቱ በነበረው ባህልና የአኗኗር ዘይቤ ውስጥ የተለመደ፣ አክብሮትና ትሕትና የተሞላ አጠራር እንደነበር ከቅዱስ መጽሐፍ እንረዳለን፡፡ በወንጌል ውስጥ በተለያየ ቦታ ኢየሱስ የሴቶችን እምነት ሲያደንቅ፣ የእርሱን ማንነት ያልተገነዘቡ ሴቶች ሲያስተምር፣ ሲፈውሳቸውና ሲያጽናናቸው የተጠቀመው ቃል ነው(ማቴ 15፡ 28፤ ሉቃ 13፡ 12፤ ዮሐ 4፡ 21፤ ዮሐ 8፡ 10፤ ዮሐ 20፡ 15)፡፡ በተጨማሪም ይህ ቃል ስምዖን ጴጥሮስ እንዲሁም መላእክትም ተጠቅመውበታል(ሉቃ 22፡ 57፤ ዮሐ 20፡ 13)፡፡

ኢየሱስ ሞቶ ከተቀበረ በኋላ ልብዋ በኀዘን ተሞልቶ ኢየሱስን ፍለጋ ወደ መቃብሩ ለሄደችው ለመግደላዊት ማርያም በመጀመሪያ መላእክት ቀጥሎም ከሙታን የተነሣው ኢየሱስ መቃብሩ ቦታ ላይ ሆነው “አንቺ ሴት! ለምን ታለቅሻለሽ?” በማለት ጠይቀዋታል (ዮሐ 20፡ 13-14)፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም ሴቶችን ሲመክር “አንቺ ሴት !” በማለት ተናግሮአል (1 ቆሮ 7፡ 16)፡፡ 

ይህን ቃል ኢየሱስ በተልእኮው መጀመሪያ ላይ ማለትም የመጀመሪያው ተአምር በሚያከናውንበት ቦታ ላይ(ዮሐ 2፡ 4) እና በተልእኮው መጨረሻ ወይም መደምደምያ ላይ መስቀል ላይ እንደተቸነከረ እናቱን ለመጥራት ተጠቅሞበታል፡፡ ይህም ማለት ኢየሱስ ማንነቱን በብዙዎች ዘንድ መታወቅ የጀመረበት ሰዓትና ለሁሉም ከፍ ብሎ መሰቀሉን በተረጋገጠበት ወቅት ላይ ይህች ሴት ከጐኑ አለች፡፡ ስለዚህ ይህች ሴት በኢየሱስ የማዳን ሥራ ውስጥ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ተገኝታለች፡፡ በመሆኑም ንቀት፣ ክብር ማጉደል፣ ትኩረት አለመስጠትና ከእርሱ እንድትርቅ የሚያደርግ መንፈስ ማንጸባረቅ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ኢየሱስም ሆነ መላእክት እንዲሁም ሐዋርያት ለሁሉም ሴቶች፣ በሁሉም ስፍራ ለመጥራት የተጠቀሙበት ቃል ነው፡፡

ኢየሱስ የመጀመሪያው ተአምር በሚያከናውንበትና በመስቀል ላይ ሆኖ የመጨረሻው የማዳን ሥራ በሚሠራበት ሰዓት “አንቺ ሴት” ብሎ የጠራትን እናቱ መገኘትዋ ማርያም እንደ “አዲሲትዋ ሔዋን” ሆና መቅረብዋን የሚያሳይ ነው፡፡ በተጨማሪም አዳም ለሔዋን እነሆ እኔኑ የምትመስል አገኘሁ፤ ከአጥንቴ የተገኘች አጥንት ናት፤ ከሥጋዬ የተገኘች ሥጋ ናት፤ ከወንድ የተገኘች ስለሆነ ሴት ትባል” አለ (ዘፍ 2፡ 23)፡፡ 

በእርግጥ በመጀመሪያዪቱ ሴት አማካይነት ሞት ወደ ዓለም ገብቶአል፡፡ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ደሙን አፍስሶ ሲሞት የክፋት አባት ምልክት የሆነውን ራሱን ሙሉ በሙሉ ተቀጥቅጦአል፤ በዚያ ወሳኝ በሆነ የመስቀል ሞትና የማዳን ሥራ ወቅት የኢየሱስ እናት “አንቺ ሴት” በሚል መልኩ ተጠርታለች፡፡ ስለዚህ “አንቺ ሴት” የሚለው ቃል የመጀመሪያው የፍጥረት ታሪክ እያስታወሰ አዲሲትዋ ሔዋን በሰዎች የደኅንነት ታሪክ ጅማሬ ላይ የተጫወተችውን ሚና ለማስገንዘብ የገለጸው ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡

❖ “ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?” የሚለው እንዴት እንረዳዋለን?

  ኢየሱስ “ከአንቺ ጋር” በሚልበት ጊዜ ራሱን ከሥጋዊ ዝምድና ውስንነት ለመለየትና መለኮታዊ መሆኑን ለመግለጽ የተጠቀመበት ይመስላል፡፡ ይህም ማለት እርሱ ማከናወን ያለበት የማዳን ሥራ በምንም ዓይነት መልኩ በሰብአዊ አመለካከት ሳይወሰን የእግዚአብሔር አብ ፈቃድ እያደመጠ የሚከናወን መሆኑን ለመግለጽ ይመስላል፡፡ እርሱና እግዚአብሔር አብ ብቻ እየተነጋገሩ የሚከናወን ተግባር ነው፡፡ “እነሆ እናትህና ወንድሞችህ እኅቶችህም በውጪ ቆመው ይፈልጉሃል” ባሉት ጊዜ “እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” ካለ በኋላ “የእግዚአብሔር ፈቃድ የሚፈጽም ሁሉ እርሱ ወንድሜም፣ እኅቴም እናቴም ነው” በማለት መለሰላቸው (ማር 3፡ 33፤ ሉቃ 8፡ 21)፡፡ 

  ስለዚህ ኢየሱስ ሁሌም ቤተሰብ ወይም ማኅበረሰብ ወይም ዘመዶችህ ከሚለው ጠባብና ሰብአዊ አመለካከት መውጣት ይፈልጋል፤ በእምነት ሁሉም የእግዚአብሔር ልጅ የሚሆንበት በር ይከፍታል፡፡ ምንም እንኳ እንደ ሰዎች ሥጋ ለብሶ ከሰው ቢወለድም መለኮታዊ ነው፤ ለዓለም ሕዝብ ሁሉ መዳን የተሰጠ ነው፤ ወዳጅነቱ፣ አገልግሎቱ፣ ጠቅላላ ሕይወቱ ለሁሉም የሁሉም ነው፡፡ ስለዚህ የእርሱ ማንነትና ተግባር በሰዎች አመለካከትና ጠያቂነት ሳይሆን በእግዚአብሔር አብ ፈቃድ የሚወሰን ነው፡፡

በአጠቃላይ ይህንን አነጋገር የተጠቀመው ኢየሱስ እናቱን የሚንቅና አክብሮት የማይሰጥ ሆኖ አይደለም፡፡ ምንም እንኳ የእግዚአብሔር ልጅ ቢሆንም ለማርያምና ለዮሴፍ እየታዘዘ ያደገ ነው (ሉቃ 2፡ 51)፡፡ በአይሁዳውያን እምነትም ሆነ ባህል ወላጅ ማክበር የጥሩ ሥነ ምግባራዊ ሕይወት መገለጫ ነው፤ እግዚአብሔርም አባትህንና እናትህን አክብር፤ ይህን ብታደርግ እኔ በምሰጥህ ምድር የረዥም ዘመን ዕድሜ ይኖርሃል ብሎአል(ዘጸ 20፡ 12፤ ዘዳ 27፡ 16)፡፡ 

ኢየሱስ በተለያየ ጊዜ ሰው ወላጁን ማክበር እንዳለበት ደጋግሞ ተናግሮአል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም ወላጅን ማክበር የጥሩ ሥነ ምግባራዊ ሕይወት ውጤት እንደሆነ አስተማረ (ኤፌ 6፡ 2-3)፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ እናቱን እንደሚያከብርና እንደሚያደምጥ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ የለም፤ አሁን ግን በእግዚአብሔር አብ የተፈቀደው ጊዜ ስላልደረሰ “ጊዜዬ ገና አልደረሰም እኮ” በማለት ይመልስላታል፡፡ 

ይህም ማለት “አሁን በዚህ ጉዳይ ውስጥ እንድገባ ለምን ትገፋፊኛለሽ? ሁሉን ነገር በእግዚአብሔር ፈቃድ በጊዜው ይከናወናል፤ ይህንን ነገር አሁን እፈጽመው ዘንድ ጊዜዬ አልደረሰም” እንደማለት ነው፡፡ በተጨማሪም እዚህ ታሪክ ውስጥ ኢየሱስ ልዩ ትኩረት የሰጠው ጥያቄውን ነው እንጂ ስለ ጠያቂው ግለሰብ አይደለም፡፡ የተጠየቀው ጥያቄ ከእርሱ የአገልግሎት ተግባር ክንውን ጋር ማለትም ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር የተመቻቸ ላይሆን ይችላል፤ ስለዚህም ለተጠየቀው ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል፡፡ ምላሹም “ጊዜዬ አልደረሰም እኮ” የሚል ነው፡፡
     

❖ “ጊዜዬ ገና አልደረሰም እኮ!” የምን ጊዜ ወይም የትኛውን ጊዜ ነው?

  በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ኢየሱስ በተለያየ ጊዜ “ጊዜው እንዳልደረሰ” ይናገራል፡፡ የይሁዳ ባለሥልጣናት ሊይዙት ሲፈልጉት በነበረበት ወቅት ለዳስ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ አልፈለገም፤ ምክንያቱም “ጌዜዬ ገና ስላልደረሰ” በማለት ይገልጻል(ዮሐ 7፡ 6-8)፡፡ ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውስጥ ሲያስተምር ሊገድሉት የሚፈልጉ ሰዎች ሊይዙት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን “ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም አልያዘውም” ይላል(ዮሐ 7፡ 30)፡፡ ኢየሱስ የዓለም ብርሃን ስለመሆኑ እያስተማረና እየመሰከረ በነበረበት ወቅት ፈሪሳውያን ሊይዙት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን “ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም አልያዘውም” ይላል(ዮሐ 8፡ 20)፡፡ ይህ በተደጋጋሚ በተለያየ መልኩ “ጊዜዬ አልደረሰም” ወይም “ጊዜው አልደረሰም ነበር” በማለት የተገለጸው የትኛውን ጊዜ የሚያመለክት ነው? ይህንን ጊዜ በማን የሚመራ ነው?

ኢየሱስ “ጊዜዬ አልደረሰም” በማለት የገለጸው መስቀል ተሸክሞ፣ ደሙን አፍስሶ፣ ሕይወቱን በመስቀል አሳልፎ በመስጠት የማዳን ሥራውን የሚያጠናቅቅበትና የሚከብርበት ጊዜ ማለት ነው፡፡ ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ሲወጣ ኢየሱስ “አሁን የሰው ልጅ ከበረ፤ እግዚአብሔርም እርሱን ያከብረዋል” በማለት ተናግሮአል (ዮሐ 13፡ 31-32)፡፡ 

ከዚህ የምንረዳው ኢየሱስ የሚከብርበት ጊዜ የሚጀምረው ከይሁዳ ክህደት እንደሆነ ነው፡፡ በተጨማሪም ወደ ኢየሩሳሌም በክብር በገባበትና ተላልፎ የሚሰጥበት ጊዜ በተቃረበበት ወቅት እነሆ የሰው ልጅ የሚከብርበት ሰዓት ደርሶአል በማለት ተናግሮአል(ዮሐ 12፡ 23)፡፡ ይህ ሰዓት ኢየሱስ በመስቀል አልፎ ወደ እግዚአብሔር አብ የሚመለስበት ጊዜ እንደሆነ ሲናገር ኢየሱስ “ይህን ዓለም ትቶ ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት መድረሱን አወቀ” ይላል(ዮሐ 13፡ 1)፡፡ ይህ ሰዓት “የመከራ፣ የጭንቀት፣ የሥቃይና የብቸኝነት ጊዜ” እንደሚሆን ኢየሱስ ገልጾታል(ዮሐ 12፡ 27-28)፡፡ ይህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱም የሚክዱበትና ትተውት የሚሄዱበት ጊዜም እንደሆነ ከወንጌሉ እንረዳለን(ዮሐ 16፡ 32)፡፡ ኢየሱስ ይህንን ጊዜ መድረሱን ለእግዚአብሔር አብ ሲገልጽ “አባት ሆይ ! እነሆ ሰዓቱ ደርሶአል፤ ልጅህ እንዲያከብርህ ልጅህን አክብረው” ይላል (ዮሐ 17፡ 1-2)፡፡ ይህ የመከራ ሰዓት የተባለውን ከእርሱ እንዲርቅ ወደ እግዚአብሔር አብ ጸለየ(ማር 14፡ 35)፤ ስለዚህ ይህ ጊዜ በእግዚአብሔር አብ ፈቃድ የሚመራ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡  

በአጠቃላይ “ጊዜዬ አልደረሰም” ሲል የመከራ ጽዋ የሚጠጣበት፣ በመስቀል የሚያልፍበትና በእግዚአብሔር አብ ዘንድ የሚከብርበት ጊዜ ማለቱ ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ጊዜ ከመድረሱ በፊት ብዙ ተግባራት ማከናወን አለበት፤ ለሕዝቡ የሕይወት መንገድ ማሳየት አለበት፤ እርሱ እውነት፣ ሕይወት፣ መንገድ መሆኑን ማስተማር አለበት፡፡ የእርሱ ማስታወሻ ይሆን ዘንድ ሥጋውንና ደሙን መስጠት አለበት፤ የእርሱ የሆኑትን ብቻቸውን እንደማይሆኑና መንፈስ ቅዱስ መጥቶ እንደሚያበረታቸው ማስገንዘብ አለበት፡፡

የኢየሱስ ጊዜ በእግዚአብሔር አብ ፈቃድ ውስጥ ያለ ነው፤ ይህንን ምድራዊ ጊዜ በመስቀል ሞት ይጠናቀቅና ዘላለማዊ የሆነውን ጊዜ ይጀምራል፡፡ በእርግጥ እንደ ዮሐንስ ወንጌል አገላለጽ ኢየሱስ የማስተማርና የማዳን ሥራውን በዚህ ዓለም ሲጀምር የእግዚአብሔር መንግሥት መገለጡን ይጀምራል፤ በተአምራቶቹም የክብሩን መታየት ጅማሬ ይሆናል፡፡ የመጀመሪያው ተአምር ሲያከናውን የጊዜው መድረስ ምልክት ይሆናል፤ አገልግሎቱን በግልጽ ይጀምራል፤ ወደ መስቀሉ በተቃረበበት ወቅት ደግሞ ኢየሱስ ራሱ እነሆ ጊዜው ደርሶአል በማለት ይናገራል (ዮሐ 17፡ 1)፡፡

❖ “እርሱ የሚላችሁን አድርጉ” ማለት ምን ማለት ነው?

  ማርያም የኢየሱስ ምላሽ ሙሉ በሙሉ የተቀበለችው ይመስላል፡፡ ሌላ ተጨማሪ ነገር አትናገረውም፤ አትጐተጉተውም፡፡ ቦታውንና ኃላፊነቱን ለኢየሱስና ለሠርጉ አስተናጋጆች በመተው ዞር ትላለች፡፡ የእርስዋ ትልቁ ተግባር ግራ ስለተጋቡት የሠርጉ አስተናጋጆች መጠየቅና ከኢየሱስ ጋር ማስተዋወቅ ነው፡፡ እነዚህ የሠርጉ አስተናጋጆችና ጠቅላላው የሠርጉ ታዳሚዎች በእስራኤል ሕዝብ ሊመሰሉ ይችላሉ፤ እስራኤላውያን የሙሴ ሕግ አላቸው፡፡ 

እስራኤላውያን አዲሱ የፍቅር ሕግ ይዞ የመጣውን መሲሕ የእግዚአብሔር ልጅ አላወቁትም፤ አሁንም አሮጌውን የሙሴ ሕግ ይዘው ቆይተዋል፡፡ አሁን በአዲስ ወይን ጠጅ የተመሰለ የአዲስ ኪዳን የፍቅር ሕግ በኢየሱስ መቀበል ስላለባቸው ማርያም ለእስራኤላውያን “እርሱ የሚላችሁን አድርጉ” በማለት ታስተዋውቀዋለች፡፡ እነርሱም ኢየሱስ የሚላቸውን ከተገበሩ ነፍስንና ሥጋን መንፈስንም ሁሉ የሚያረካው በአዲሱ ወይን ጠጅ የተመሰለውን የፍቅር ሕግ ይሰጣቸዋል፡፡ ስለዚህ ይህንን ይከናወን ዘንድ ማርያም የትውውቅ በሩን ከፍታ ትሄዳለች፡፡  

ከነዓናዊትዋ ሴት ስለ ልጅዋ ፈውስ ኢየሱስን ስትጠይቀው በመጀመሪያ ምንም አልመለሰላትም፡፡ ቀጥሎም የልጆች ምግብ ለውሾች መስጠት ተገቢ አይደለም በማለት እርስዋን የሚያርቅ ምላሽ ሰጣት፤ ሴትዮዋ ግን እየተከተለችውና ምላሽ እየሰጠችው የፈለገችውን እንዲፈጽምላት ጠየቀችው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ይህች ሴት እየተከተለችን ስለምትጮኽ እባክህ አሰናብታት አሉት(ማቴ 15፡ 23)፡፡ በመጨረሻም “አንቺ ሴት እምነትሽ ትልቅ ነው” አላት(ማቴ 15፡ 21-28)፡፡ ማርያም ግን ኢየሱስ የሰጣትን ምላሽ በትሕትና ተቀብላለች፡፡ ምክንያቱም ኢየሱስ በመለኮታዊ ፈቃድ መመራት እንዳለበትና የእርስዋ ልጅ ብቻ ሳይሆን የሁሉምና ለሁሉም የተሰጠ መሆኑን ተገንዝባለች፡፡ 

በመሆኑም ለሠርጉ አገልጋዮች “ልጄ የሚላችሁን አድርጉ” ሳይሆን “እርሱ የሚላችሁን አድርጉ” ትላቸዋለች፡፡ ይህ አባባል በመጀመሪያ የማርያምን እምነት ወይም ማርያም በኢየሱስ ላይ ያላት መተማመን የሚያሳይ ነው፡፡ እርሱ በዚህ በችግር ወቅት አንድ ነገር ማድረግ እንደሚችል እርግጠኛ ስለሆነች በሙሉ መተማመን እርሱ የሚላቸውን እንዲተገብሩ ታሳስባቸዋለች፡፡ ቀጥሎም የሠርጉ አገልጋዮች በኢየሱስ እንዲተማመኑና መፍትሔ ከእርሱ ሊያገኙ እንደሚችሉ ትመራቸዋለች፡፡ አገልጋዮችም ልክ እስራኤላውያን የሙሴ ሕግ ከተቀበሉ በኋላ እግዚአብሔር ያዘዘንን ሁሉ እንፈጽማለን በማለት ይዘጋጁ እንደነበረው ሁሉ የኢየሱስን ትእዛዝ ለማከናወን ተዘጋጁ(ዘጸ 19፡ 8፤ 24፡ 7)፡፡ 

በሌላ በኩል “እርሱ የሚላችሁን አድርጉ” የሚለውን ንግግር የግብጽ ንጉሥ የነበረው ፈርዖን ለሕዝቡ የሰጠው መመሪያ ነበር፡፡ ግብጻውያን ረሀብና ጥማት በዝቶባቸው በችግር ውስጥ ይንገላቱ በነበረ ጊዜ ወደ ፈርዖን ሄደው “ምግብ ስጠን” ብለው ጮኹ፡፡ ፈርዖንም ወደ ዮሴፍ ሂዱና እርሱ የሚላችሁን አድርጉ ብሎ አዘዛቸው(ዘፍ 41፡ 55)፡፡ ዮሴፍም ጐተራዎች ሁሉ ተከፍተው እህሉ ለግብጻውያን ጥቅም እንዲውል አደረገ(ዘፍ 41፡ 56)፡፡ ዮሴፍ በግብጽ ውስጥ በአስተዳዳሪነት ሲሾም የንጉሡ የወርቅ ጣት አጠለቁለት፤ ከሐር የተሠራ ልብስ አለበሱት፤ በአንገቱም የወርቅ ሐብል አደረጉለት፤ በንጉሡ ሁለተኛ ሠረገላ እንዲቀመጥ አደረጉት፤ የንጉሡም የክብር ዘብ ከፊት ፊት እየሄደ “እጅ ንሡ ! እጅ ንሡ ይል ነበር” (ዘፍ 41፡ 42-43)፡፡ ፈርዖን ስለ ዮሴፍ ሲመሰክር “የእግዚአብሔር መንፈስ ካደረበት ከዮሴፍ የተሻለ ሰው ከቶ አናገኝም” አላቸው(ዘፍ 41፡ 38)፡፡ በአጠቃላይ ዮሴፍ ትልቅ ሥልጣንና ክብር ተቀዳጅቶ በአገሪቱ ውስጥ ማስተዳደር የጀመረ ሰው ነበር፡፡ 

  በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ የሠርጉ አስተናጋጆች ወይን አልቆባቸው ግራ ተጋብተዋል፤ ማርያም ደግሞ “እርሱ የሚላችሁን አድርጉ” በማለት ወደ ኢየሱስ ትመራቸዋለች፤ ከኢየሱስ ጋር ታስተዋውቃቸዋለች፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ግብጻውያን ምግብ አልቆባቸው ወደ ፈርዖን ሲጮኹ “እርሱ የሚላችሁን አድርጉ” በማለት ወደ ዮሴፍ ላካቸው፤ ከዮሴፍ ጋር አስተዋወቃቸው፡፡ ዮሴፍ ምንም ዓይነት ክፋት ሳይሠራ መላው እስራኤልን በሚወክሉ በዐሥራ አንድ ወንድሞቹ ተነቀፈ፤ ታደመበት፤ በጉድጓድ ተጣለ፤ በመጨረሻም ለግብጻውያን ተሸጠ፡፡ 

ኢየሱስም ወደፊት በሕዝቡ ይነቀፋል፤ መከራ ይደርስበታል፤ በገንዘብ ተላልፎ ይሰጣል፡፡ ስለዚህ ማርያም “እርሱ የሚላችሁን አድርጉ” በምትልበት ጊዜ ኢየሱስን እንደ አዲሱ ዮሴፍ እያየችው ሊሆን ይችላል፡፡ ማርያም ሁሉን ነገር አስቀድማ ተረድታው ነበር፤ በልብዋም ታሰላስለው ነበር(ሉቃ 2፡ 51)፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ሕዝቡን ከዘላለማዊ የመንፈስ ረሀብና ጥማት የሚያድንና ዘላቂ የሆነ መፍትሔ የሚሰጥ መሲሕ ነው፡፡ በእርግጥ ኢየሱስ “እኔ የሕይወት እንጀራ ነኝ”፤ “እኔ የሕይወት ውሃ ነኝ” በማለት ተናግሮአል(ዮሐ 6፡ 48፤ 7፡ 37-39)፡፡ 

❖ “ስድስቱ ጋኖች” ትርጓሜአቸው ምንድን ነው?

በቃና የሠርግ ግብዣ ላይ አይሁዳውያን የመንጻት ሥርዓት ስለነበራቸው ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ እንደነበሩ ተገልጿል(ዮሐ 2፡ 6)፡፡ በአይሁዳውያን ቋንቋና እምነት አገላለጽ ስድስት ቁጥር ጉድለትን ያሳያል፤ ሰባት ደግሞ የፍጽምና ወይም ሙልአትን መገለጫ ነው፡፡ ስለዚህ “ስድስት የድንጋይ ጋኖች ነበሩ” ሲል ሠርጉ ላይ የነበረውን ክፍተትና ጉድለት ከማሳየት አኳያ የተጠቀሰ ይመስላል፡፡ የጋኖቹ ውሃ የመያዝ አቅም ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ያህል መሆኑን መገለጹን ብዛቱን ከማሳወቅ አኳያ የተነገረ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም ኢየሱስ ወደ ወይን ጠጅ ቀይሮ ለሠርጉ አስተናጋጆች የሰጣቸውን የወይን ጠጅ መጠን እጅግ በጣም ብዙና ጥሩ ከመሆኑ የተነሣ ብዙዎች እስከሚረኩ ድረስ መጠጣት የሚያስችላቸው እንደነበር ለመግለጽ ነው፡፡ 

ጋኖቹ በኢየሱስ ትእዛዝ መሠረት ውሃ እስከ አፋቸው ተሞልተዋል፤ አገልጋዮቹም ምንም እንኳ የኢየሱስ ማንነት ባያውቁትም “እርሱ የሚላችሁን አድርጉ” በተባሉት መሠረት በጸጥታ እየታዘዙ ተግባራቸውን ማከናወኑን ቀጥለዋል፡፡ ኢየሱስ የሠርጉ ግብዣ አስተናጋጆች ማዘዙን በመቀጠል በሉ አሁን ቀድታችሁ ለግብዣው ኃላፊ ስጡት አላቸው (ዮሐ 2፡ 8)፡፡ 

አዲሱ የወይን ጠጅ በጥሩነቱ ብቻ ሳይሆን እስከ መጨረሻ ድረስ አለማለቁና ከየት እንደመጣ የግብዣው ኃላፊ አለማወቁ ተጠቅሶአል፡፡ በእርግጥ የወንጌላዊው ዋና ትኩረት ማርያም የሰዎቹን ችግር ይዛ ወደ ኢየሱስ መቅረብዋን፣ ኢየሱስ በሥጋዊ ቤተሰብ ፈቃድ ሳይሆን በእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሚመራና ምንም እንኳ ጊዜው ባይደርስም በማርያም የተጠየቀውን ማከናወኑ ላይ ነው፡፡ በተጨማሪም ከውሃ ወደ ወይን ጠጅ የተለወጠውን አዲሱ ወይን ጠጅ በብዛቱና በጣዕሙ እጅግ በጣም ብዙና የተሻለ እንደነበርና ኢየሱስ ክብሩን እንደገለጠ ማስገንዘብ ነው፡፡ 

በታሪኩ መጨረሻ ላይ ዋናው የወንጌላዊው ልዩ ትኩረት የሆነው ግን የደቀ መዛሙርቱ በኢየሱስ ማመን ነው(ዮሐ 2፡ 11)፡፡ በዮሐንስ ወንጌል የተጠቀሱት ተአምራት አብዛኞቹ ዋና ዓላማቸው ወይም ከተአምራቱ በኋላ ልዩ ትኩረት የሚያደርገው ሕዝቡም ሆነ ደቀ መዛሙርቱ “ኢየሱስ መሲሕ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ማሳወቅ ላይ ነው”፤ ደቀ መዛሙርቱም ሆኑ ሕዝቡ ማመናቸውን መግለጽ ነው፡፡ ይህ እምነት ከኢየሱስ ጋር ለሚያደርጉት ቆይታ ወሳኝ ነው፤ ከእርሱ ጋር ወዳጅነታቸውን ያጠናክርላቸዋል፡፡ በጥንት ዘመን ሰዎች አንድነታቸውና ሕብረታቸውን ለመግለጽ ይጠቀሙበት ከነበሩት መንገዶች ውስጥ አንዱ ወይን በጋራ መጠጣት ነበር፤ በመሆኑም ይህ ጥሩ ወይን የኢየሱስና የእግዚአብሔር አብ አንድነት እንዲሁም የኢየሱስና የደቀ መዛሙርቱ ሕብረትና ወዳጅነት ሊገልጽ እንደሚችል ይታመናል፡፡

❖ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ከእናቱና ከሚወደው ደቀ መዝሙር ጋር የተነጋገረው ምንድን ነው?

ኢየሱስ ከሁሉም በማስበለጥ ለምን ስለ እናቱና ስለሚወደው ደቀ መዝሙር ብቻ ተናገረ? የሚለው ጥያቄ በተለያየ መልኩ ምላሽ ተሰጥቶታል፡፡ በእርግጥ ማርያም እዚያ ቦታ ላይ እንደ እናት የተሰጠችው ለሚወደው ደቀ መዝሙር ብቻ ሳይሆን በሚወደው ደቀ መዝሙር አማካይነት ለተወከሉት ለሁሉም ደቀ መዛሙርት ነው፡፡ ማርያም ለሁሉም ደቀ መዛሙርት እናት ትሆን ዘንድ ተሰጠች፤ ይህም ማለት ለመላው ቤተ ክርስቲያን የተሰጠች እናት ነች፡፡ ስለዚህ ደቀ መዛሙርት ለዚህች እናት እንዲያስቡላትና እንዲንከባከብዋት ያስፈልጋል፤ እርስዋም እናትነትዋና የእናትነት ፍቅርዋ ለሁሉም ታበረክታለች፡፡ 

ነቢዩ ኢሳይያስ ስለ ጽዮን ሲናገር እንዲህ ብሎ ነበር፤ “እነዚህን ሁሉ ልጆች ማን ወለደልኝ? እኔ ብቻዬን ቀርቼ ነበር፤ እንግዲህ እነዚህ ሁሉ ልጆች ከወዴት መጡ?” (ኢሳ 49፡ 21)፡፡ በተጨማሪም ነቢዩ ስለ ጽዮን ሲናገር “ነገሥታት አባቶችሽ ይሆናሉ፤ እቴጌዎቻቸውም ሞግዚቶችሽ ይሆናሉ” ብሎ ነበር(ኢሳ 49፡ 23)፡፡ በዚህ መሠረት አዲሲትዋ ጽዮን ብዙ ልጆች ማለትም ከአይሁዳውያንና ከአረማውያን ወገን ይኖርዋታል፤ የብዙ ልጆች እናት ትባላለች፡፡ ይህች አዲስትዋ ጽዮን የኢየሱስ እናት ማርያም እንደምትሆን መስቀሉ ሥር በተገኝችበት ቅጽበት በኢየሱስ ተረጋገጠ፡፡ 

ማርያም በቃና የሠርግ ግብዣ ላይ ለኢየሱስ “ሠርገኞቹ የወይን ጠጅ የላቸውም እኮ!” ስትለው “ጊዜዬ ገና አልደረሰም እኮ” በማለት መልሶላት ነበር፡፡ አሁን ግን ያንን ጊዜ ደርሶአል፡፡ በመሆኑም የእናትነት ተግባር የምታከናውንበትና የአገልግሎት ሚና የምትወጣበት ኃላፊነት አሁን ጊዜው ደርሶ በመስቀል ላይ ከተቸነከረው ከልጅዋ ትቀበላለች፡፡ የሁሉም እናት ወይም አዲሲትዋ እስራኤል በመሆን ሁሉንም አይሁዳውያንም አረማውያንም እጆችዋን ዘርግታ ትቀበላለች፤ የኢየሱስ ሆነው እንዲኖሩ በርዋን ትከፍትላቸዋለች፡፡ ስለዚህ “እናቴ ሆይ! እነሆ ልጅሽ” በማለት ያልወለደችውን፤ ነገር ግን ሁሉም ደቀ መዛሙርት ከመወከሉም አልፎ ወደፊት የእርስዋ ልጆች የሚሆኑትንም ሁሉ ወክሎ የተገኘውን ደቀ መዝሙር ትቀበላለች፡፡ 

ኢየሱስ በመስቀል ላይ መሥዋት እስከሆነበት ደቂቃ ድረስ የእረኝነት ተግባሩን ተወጥቶአል፤ አሁን ሁሉም ነገር በሚጠናቀቅበት ወቅት ደግሞ እናቱን የሁሉም እናት ትሆን ዘንድ ይሰጣል፡፡ ኢየሱስ በዚያን ወሳኝ በሆነው ሰዓት ለሚወደው ደቀ መዝሙር እናቱን መስጠቱን ለዓለም ሁሉ እንደመስጠት ነው፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ዓለም ስለወደደ ሕይወቱን ሰጠ፤ የራሱን ወገኖች እስከ መጨረሻው ድረስ ወደዳቸው (ዮሐ 13፡ 1)፤ አሁንም እናቱን ለእነርሱ በመስጠት ፍቅሩን ገለጸ፡፡

ኢየሱስ የሚወደው ደቀ መዝሙርና እናቱን አንድ እንዲሆኑ በመጨረሻው ሰዓት በኑዛዜ መልክ መናገሩን አንድ ቤተሰብ መመሥረቱን የሚያሳይ እንደሆነም ይታመናል፡፡ ማርያም ለሚወደው ደቀ መዝሙር ተሰጥታለች፤ እርሱም ያስብላታል፤ ወደ ቤቱም ይወስዳታል፡፡ የሚወደው ደቀ መዝሙርም እናት የምትሆነውን ተሰጥቶታል፤ እርስዋም የእናትነት ፍቅርዋን ትገልጽለታለች፤ እንደ እናት ሆናም ትንከባከበዋለች፡፡ ስለዚህ ይህ የተመሠረተው ቤተሰብ ዋና መተሳሰሪያው ቤተሰባዊ ፍቅር ነው፡፡ 

የመጀመሪያዋ ሔዋን የወለደችውን አቤል ምንም ዓይነት በደል ሳይፈጽም በቃየል በተገደለ ጊዜ ሌላ ልጅ ተሰጣት፤ እርስዋም ቃየል በገደለው በአቤል ምትክ እግዚአብሔር ወንድ ልጅ ሰጠኝ ስትል “ሤት” ብላ ጠራችው (ዘፍ 4፡ 25)፡፡ አዲሲትዋ ሔዋንም ልጅዋ ኢየሱስ በሰዎች ፍርድ ተላልፎ ተሰጥቶ በሚሞትበት ቅጽበት ሌላ ልጅ እንዲሆናት የሚወደውን ደቀ መዝሙር ተሰጣት፡፡ እርስዋም የሁሉም እናት እንድትሆን ስጦታውን ተቀበለች፡፡

የትምህርቱ አዘጋጅ፦ አባ ምሥራቅ ጥዩ (ዶ/ር)